በመንግስት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በተሳካ ሁኔታ ተከናወነ
በመንግስት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በተሳካ ሁኔታ ተከናወነ
አዲስ አበባ — የመንግስት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር በሀገር አቀፍ ደረጃ የተያዘውን የ800 ሚሊዮን የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ ብሔራዊ መርሃ-ግብር በስኬት ማጠናቀቁን አስታወቀ። አስተዳደሩ ባወጣው የክንውን ሪፖርት መሠረት፣ በዕለቱ የታቀደውን ግብ 100% በላይ በማሳካት አጠቃላይ 9,230 ችግኞችን መትከል ችሏል።
በዚሁ የአንድ ጀምበር መርሃ-ግብር ላይ የአስተዳደሩን ዋና መሥሪያ ቤት እና ዘጠኝ ሪጅኖችን ጨምሮ በአጠቃላይ 727 ሠራተኞች በቀጥታ ተሳትፈዋል። ተቋሙ ለሠራተኞቹ ሙሉ የትራንስፖርት፣ የውሃ እና የምግብ አቅርቦት ያመቻቸ ሲሆን፣ ሂደቱም በከፍተኛ አመራሮች በተዋቀረ አስተባባሪ ኮሚቴ እና በቡድን መሪዎች የቅርብ ክትትል ሲደረግበት ውሏል።
መጀመሪያ ላይ ለመትከል የታቀደው 8,830 ችግኞችን የነበረ ቢሆንም፣ ተጨማሪ 400 ጉድጓዶችን በማዘጋጀት አፈጻጸሙን ማሳደግ ተችሏል። በተከላው ላይ እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ቡና፣ ጥድ እና ዋንዛ ያሉ የተለያዩ የኢኮኖሚና የአካባቢ ጥበቃ ጠቀሜታ ያላቸው የችግኝ ዓይነቶች በየክልሉ ተተክለዋል።
የሪጅኖች አፈጻጸምን በተመለከተ ደቡብ ሪጅን እና ምዕራብ ሪጅን እያንዳንዳቸው 1,500 ችግኞችን በመትከል ቀዳሚነቱን የያዙ ሲሆን፣ ምስራቅ ሪጅን 1,300 እንዲሁም ሰሜን ምስራቅ ሪጅን 1,200 ችግኞችን አሳክተዋል። ዋና መሥሪያ ቤትና አዲስ አበባ ሪጅንን ጨምሮ ሌሎች የአስተዳደሩ መዋቅሮችም በተመደቡባቸው ቦታዎች ሁሉ ችግኞችን በስኬት መትከላቸው ተገልጿል።
ተቋሙ በማጠቃለያው፤ ይህንን ሀገራዊ ጥሪ ለመመለስና የአረንጓዴ አሻራ ግብን ለማሳካት ሁሉንም ሪጅኖች ያሳተፈ የተቀናጀ ርብርብ መደረጉን ገልጾ፣ መርሃ-ግብሩ በታቀደው መልኩ በድል መጠናቀቁን አረጋግጧል።