አስተዳደሩ በባህርዳር ከተማ ጧሪ ለሌላቸው አረጋውያን ያሰራቸውን ቤቶች አስረከበ

የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አረጋውያን በባህርዳር ከተማ ያስገነባቸውን 14 ቤቶች ጥር 21 ቀን 2018 የባህርዳር ከተማ አስተዳደር አካላትና የጡረተኞች ተወካዮች በተገኙበት በማስመረቅ ለባለቤቶቹ አስረከበ።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን በቀለ እንዳሉት አስተዳደሩ ከመደበኛ ስራው ጎን ለጎን ዘርፈ ብዙ የማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። አስተዳደሩ የተለያዩ አጋር አካላትን በማስተባበር እንደዚህ አይነት የበጎ አድራጎት ስራዎችን ይሰራል። እነዚህ ለአረጋውያንና ለአቅመ ደካማ የጡረታ ባለመብቶች የተገነቡት 14 ቤቶችም ከኮንትራክተር ጀምሮ የተለያዩ አጋዥ አካላትን አቅም በማስተባበር የተገነቡ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ም/ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለውም በዚህ በጀት ዓመት አስተዳደሩ ካሉት ስድስት ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ ባህርዳር የሚገኘው የሪጅን ጽ/ቤት ህንጻ ሲሆን፣ ሌሎችም በጅማ በሀዋሳ እና በአዲስ አበባ የሚገኙ ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጡ ህንጻዎችም ይመረቃሉ ብለዋል። 

የነዚህ ቤቶች ተጠቃሚ የሚሆኑት ሀገራቸውን በተለያዩ መስኮች ሲያገለግሉ የነበሩ፣ ለሀገር ነጻነት ደማቸውን ያፈሰሱ ባለውለታዎች ናቸው ያሉ ሲሆን፣ አስተዳደሩ በቀጣይም አቅም በፈቀደ መጠን እንደዚህ አይነት ስራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል። ለነዚህ ቤቶች ግንባታ ቦታ በማቅረብ ትብብር ያደረጉ የባህርዳር ከተማ እና የጣና ክ/ከተማ አስተዳደር አካላት እንዲሁም በነዚህ ቤቶች ግንባታ ስራ ላይ በተለያየ ደረጃ ተሳትፎ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የባህርዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ ብርሃን ንጉሴ እንዳሉት የመንግስት ሠራተኞች በስራ ላይ እያሉ ከሚከፈላቸው ደመወዝ እየተቀነሰ በቀሪ ዘመናቸው ጉልበታቸው ሲደክም፣ አቅም ሲያንሳቸውና ጡረተኛ ሲሆኑ ካዋጡት መዋጮ ተቀንሶ እስከ ህይወታቸው መጨረሻ ገቢ እንዳያጡ ታልሞበት የሚሰራ ፈንድ ነው ብለዋል። አስተዳደሩም ባህርዳር ከተማን መርጦ እነዚህን ቤቶች በመገንባት ሀገርን ላገለገሉ አረጋውያንና አቅመ ደካሞች በማስተላለፉ በከተማ አስተዳደሩ ስም እናመሰግናለን ብለዋል። 

የቤቶቹን ግንባታ ወጪ በተመለከተ ሪፖርት ያቀረቡት የአስተዳደሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ዘውድነሽ ለገሠ በበኩላቸው ቤቶቹ ሳሎን እና መኝታ ያላቸው፣ የጋራ የምግብ ማብሰያ፣ ሻወርና መፀዳጃ ቤት ያላቸው ሲሆን፣ አስፈላጊ የሆኑ የቤት ቁሳቁሶችም ጭምር የተሟላላቸው ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከ24 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸዋል ብለዋል።

የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ጽ/ቤት የጡረተኞች ተወካይ መቶ አለቃ ሲሳይ ብርሃኑ እንዳሉት የተለያዩ ስራዎችን ከሪጅን ጽ/ቤቱ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸው፣ አስተዳደሩ ለአረጋውን የሰራው ስራ ምሳሌ የሚሆን በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የቤት ባለዕድል የሆኑት በሰጡት አስተያየት ኑሯቸው በችግር ውስጥ መሆኑንና ደጋፊም እንደሌላቸው የተናገሩ ሲሆን፣ አስተዳደሩ ለዚህ ዕድል ስላበቃቸው እጅግ መደሰታቸውን እና ብዙ ችግር እንደተቃለለላቸው ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል።

Share this Post