አስተዳደሩ ከመንግስት አሰሪ መ/ቤቶች ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ
አዲስ አበባ —ነሐሴ 21/2018
የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር በጡረታ አዋጅ 1267/2014 እና በአፈጻጸም መመሪያው ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር በተደረገ የምክክር መድረክ ላይ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የገቢ አሰባሰብ ስርዓት ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል አሰራር ለመቀየር የሚያስችሉ ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑ ተገለጸ።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን በቀለ እንዳሉት፣ በተቋማት በኩል የሚታዩ የመረጃ መዛባቶች፣ በወቅቱ መዋጮ አለማስገባት እና ተገቢ ያልሆኑ አሰራሮች በተገልጋዮች ላይ እንግልት በመፍጠር የመልካም አስተዳደር ችግር ሲፈጥሩ ቆይተዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ ወደ 8 ሺህ 700 የሚጠጉ የመረጃ መዛባቶች ታይተዋል ያሉት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ ይህም የመልካም አስተዳደር ችግር ሲፈጥር ቆይቷል ብለዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የጡረተኞችን መረጃ ከፋይዳ መታወቂያ ጋር እንዲያያዝ በመደረጉ ከአንድ በላይ የጡረታ አበል የሚቀበሉ ሰዎችን በመለየት የማጭበርበር ድርጊቶችን በመከላከል ረገድ ትልቅ ውጤት አምጥቷል። ከአሁን በኋላ የሚደረጉ አዳዲስ የምዝገባ ጥያቄዎች በሙሉ ከፋይዳ መታወቂያ ጋር ተያይዘው ሊቀርቡ ይገባል ብለዋል።
አስተዳደሩ አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመንም ደረጃውን የጠበቀ የዳታ ሴንተር የገነባ ሲሆን፣ እያለማ ያለውን WINSAAS አዲስ ሲስተም ሲጠናቀቅም የምዝገባ እና የገቢ አሰባሰብ ሙሉ በሙሉ ኦንላይን (በዲጂታል) ይከናወናል።
በሌላ በኩል፣ በአንዳንድ አሰሪ መስሪያ ቤቶች በኩል የጡረታ መዋጮን በወቅቱ አለማስገባትና ህገ-ወጥ አሰራሮችን የመከተል ችግሮች እንደሚታዩ ተገልጿል። በተለይም ጥቂት የልማት ድርጅቶች አካውንታቸው እንዳይታገድ በርካታ ህገ-ወጥ የባንክ አካውንቶችን በመክፈት ሲንቀሳቀሱ የተደረሰባቸው ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ለግማሽ ቀን በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ በምዝገባ፣ በጡረታ አበል ውሳኔ፣ በጡረታ መዋጮ አሰባሰብ፣ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ የልከፈሉ ተቋማት ሀብትን ስለመያዝና ስለመሸጥ እና ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል።