የሠንደቅ ዓላማ ቀን አዲስ የመንግሥት ምሥረታ በተካሄደበት አገራዊ ምዕራፍ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል — ወ/ሮ ዘውድነሽ ለገሠ
19ኛው የሠንደቅ ዓላማ ቀን አዲስ የመንግሥት ምሥረታ በተካሄደበትና አዲስ አገራዊ ምዕራፍ በተጀመረበት ማግስት የሚከበር በመሆኑ ዘንድሮን ልዩ እንደሚያደርገው የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የዋና ስራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ዘውድነሽ ለገሠ ገለጹ።
ኃላፊዋ አያይዘውም ሠንደቅ ዓላማ የብሔራዊ ማንነት ማኅተም፣ የሉዓላዊነት ሕያው ምስክርና የነፃነት አርማ መሆኑን ጠቁመው፤ አባቶችና እናቶች በሰንደቅ ዓላማው ሥር ሆነው አገራዊ አንድነትንና ነፃነትን ጠብቀው ማቆየታቸው ኢትዮጵያን የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ፋና ወጊ እና የአፍሪካውያን የኩራት ተምሳሌት አድርጓታል ብለዋል።
አዲሱ የመደመር መንግሥት ያለፉ መልካም ተሞክሮዎችን ማስቀጠልን፣ ክፍተቶችን ማረምን እና አዳዲስ አሳቦችን ማከልን ማዕከል ያደረገ አገር በቀል እሳቤ መሆኑንም አብራርተዋል።
በመጨረሻም፣ ወቅታዊ ውስብስብ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችን በመቋቋም የጀመርነውን የብልጽግና ጉዞ ለማስቀጠል ሁሉም በተባበረ ክንድ ሊቆም እንደሚገባ ጥሪ ያቀረቡት ወ/ሮ ዘውድነሽ፤ አስተዳደሩ በ2019 በጀት ዓመት የጡረታ አቅድን የማጠናከር፣ የባለመብቶችን ገቢ የማሻሻል እና የፈንዱን ቀጣይነት የማረጋገጥ ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ ሠራተኞች ኃላፊነታቸውን በላቀ የአገልግሎት ስሜት እንዲወጡ አሳስበዋል።
በበዓሉ አከባበር ላይ የአስተዳደሩ አመራሮች፣ የስራ ኃላፊዎች እና ሰራተኞች ተገኝተዋል።