የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር ለሁሉም ሠራተኞቹ የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጠ

 
አዲስ አበባ — የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር በዋና መሥሪያ ቤት፣ በሪጅን እና በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ለሚገኙ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች አጭር የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጠ።
 
በሁለት ዙር ለሦስት ተከታታይ ቀናት (ከህዳር 1 እስከ 3 ቀን 2019 ዓ.ም. ድረስ) በቪዲዮ ኮንፈረንስ በተካሄደው በዚህ የስልጠና መድረክ ላይ፣ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአስተዳደሩ የኮርፖሬት ሪሶርስ ማኔጅመንት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን በቀለ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ በሚታዩ የአፈጻጸም ክፍተቶችን በመተንተን የተቋሙን አጠቃላይ አቅም ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
 
በኦዲት እና በክትትል ግምገማዎች የሚነሱ ክፍተቶች እና ችግሮች በቀጣይ ስድስት ወራት አፈጻጸም ሲገመገሙ ተቀርፈው የተሻለ ተቋማዊ ውጤት ሊመዘገብ እንደሚገባ አሳስበዋል። አክለውም ሥራዎችን በቴክኖሎጂ በመደገፍና የዲጂታል ክህሎትን በማዳበር የተሻለ አሠራር መዘርጋት እንደሚገባ የገለጹ ሲሆን፣ ሠራተኞችና ኃላፊዎች በባለቤትነት ስሜትና በቅንጅት በመስራት የተሰጠውን ሥልጠና ውጤት በሥራ ላይ እንዲያውቁ ጥሪ አቅርበዋል።
 
በስልጠና መድረኩ ላይ የተገኙትና «ከምላሽ ሰጪነት ወደ ቅድመ-ዝግጁነት» በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ሠነድ ላይ ስልጠና የሰጡት የአስተዳደሩ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሸዋንግዛው ታየወርቅ፤ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት፣ የሥራ ቅንነትን ማሳደግ፣ ተቋማዊ ቅንጅትን ማጠናከርና የመደጋገፍ ባህልን መገንባት የስልጠናው ዋና ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል።
 
አሠራራችንን ለማሻሻልም የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት እና ሳይንሳዊ የመረጃ ጥራት ሕግን መተግበር ሁላችንም ልንከተለው የሚገባ የአሠራር ስልት ነው ያሉት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በቀጣይ ጠንካራ የተጠያቂነት አሠራር የተዘረጋ በመሆኑ ከልማድ እስረኝነት መውጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።
 
ለዚህም የሥራ ቅንነትን፣ የቡድን ሥራ ቅንጅትና የጋራ ኃላፊነትን እንዲሁም መልካም የሥራ ግንኙነትን በመፍጠር የሚያጋጥሙንን ችግሮች መፍታት ይኖርብናል ሲሉ አክለዋል።
 
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም ስልጠናው በአሠራር፣ በባህሪና በአመለካከት ለውጥ እንድናመጣ የሚያግዝ በመሆኑ ወደፊትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
 
በስልጠና መድረኩ ላይ የምዝገባና ጡረታ አበል ውሳኔ መመሪያ፣ የጡረታ መዋጮ ገቢ አሰባሰብ መመሪያ፣ የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና አፈጻጸም ምዘና መመሪያ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዝግጅት እና ቅድመ-ሁኔታዎች የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

Share this Post