📜 ስለ ጡረታ ዐቅድ፣ ፈንዶችና መዋጮዎች ይወቁ፡ የነገ ማኅበራዊ ዋስትናችን በአዋጅ ቁጥር 1267/2014 ማዕቀፍ ውስጥ 💼✨

📜 ስለ ጡረታ ዐቅድ፣ ፈንዶችና መዋጮዎች ይወቁ፡
የነገ ማኅበራዊ ዋስትናችን በአዋጅ ቁጥር 1267/2014 ማዕቀፍ ውስጥ 💼✨
 
የመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ ዋስትና የዕለት ተዕለት የትጋታችን እውቅና እና የነገው የሰላማዊ ሕይወታችን መሠረት ነው። በአገራችን የማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ መሠረት የዜጎችን ማኅበራዊ ፍትሕ፣ የኢንዱስትሪ ሰላም እና የደህነት ቅነሳን ለማረጋገጥ የወጣውን የመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1267/2014 መሠረት በማድረግ፣ ስለ ጡረታ ዐቅድ፣ ፈንዶች አደረጃጀትና መዋጮዎች ይበልጥ ተንትነን ግንዛቤ ለመፍጠር ዋና ዋና ነጥቦቹን በዝርዝር አቅርበናቸዋል።
 
🔹 1. የመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ ዐቅድ ስለ መቋቋም
ይህ ዐቅድ የመንግሥት ሠራተኞች በሥራ ዘመናቸው ለአገርና ለሕዝብ ላበረከቱት አገልግሎትና መስዋዕትነት እውቅና በመስጠት፣ በዕድሜ መግፋት፣ በጤና መታወክ ወይም በሥራ ላይ በሚደርስ አደጋ ምክንያት ከሥራ ሲሰናበቱ አስተማማኝ ማኅበራዊ ዋስትና እንዲያገኙ በአዋጁ በይፋ ተቋቁሟል። ሠራተኛው ራሱንና ቤተሰቡን ከኢኮኖሚያዊ ችግር ጠብቆ ክብሩን የጠበቀ ሕይወት እንዲመራ የሚያስችል ብሔራዊ ሥርዓት ነው።
 
🔹 2. የጡረታ ፈንዶች ስለ መቋቋም
ለጡረታ ዋስትና የሚሰበሰበው የጡረታ መዋጮ በአግባቡ ተሰብስቦና በሕጋዊ መንገድ አዋጭ በሆኑ ኢንቨስትመንቶች ላይ ኢንቨስት ተደርጎ ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል የራሳቸው የሕግ ሰውነት ያላቸው ሁለት የተለዩ ፈንዶች ተቋቁመዋል። እነሱም፦
የሲቪል መንግሥታዊ አገልግሎት ጡረታ ፈንድ እና
የወታደራዊ እና የፖሊስ አገልግሎት ጡረታ ፈንድ ናቸው።
 
 
🔹 3. የሲቪል መንግሥታዊ አገልግሎት ጡረታ ፈንድ መዋጮ
በሲቪል (ሲቪሊያን) መሥሪያ ቤቶች፣ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወይም ፕሮግራሞች ውስጥ የሚያገለግሉ ሠራተኞችንና ቀጣሪዎቻቸውን የሚመለከት ፈንድ ነው። በአዋጅ ቁጥር 1267/2014 አንቀጽ 10 መሠረት ወርሃዊ የመዋጮ መጠኑ በሠራተኛው ደመወዝ ላይ ተመስርቶ እንደሚከተለው ይከፈላል፦
በመንግሥት መሥሪያ ቤቱ (ቀጣሪው) የሚሸፈን፦ 11%
በመንግሥት ሠራተኛው ደመወዝ የሚከፈል፦ 7%
በድምሩ፦ 18% ለፈንዱ ገቢ ይደረጋል።
 
 
🔹 4. የወታደራዊ እና የፖሊስ አገልግሎት ጡረታ ፈንድ መዋጮ
የአገርን ሉዓላዊነትና የሕዝብን ሰላም ለማስከበር ሕይወታቸውንና አካላቸውን የሚሰጡ የጸጥታ ኃይላት (የመከላከያና የፖሊስ አባላት) የሥራ ባህሪ እጅግ ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ይህንን ታሳቢ ያደረገ የተለየ የመዋጮ ሥርዓት በአዋጁ አንቀጽ 11 ተደንግጓል። የመዋጮ መጠኑ እንደሚከተለው ነው፦
በመንግሥት መሥሪያ ቤቱ (ቀጣሪው) የሚሸፈን፦ 33%
በመንግሥት ሠራተኛው (አባሉ) ደመወዝ የሚከፈል፦ 7%
በድምሩ፦ 40% መዋጮ ለፈንዱ ገቢ ይደረጋል።
 
 
🔹 5. የጡረታ መዋጮ ክፍያ አፈጻጸምና አስተዳደር
እያንዳንዱ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የሠራተኞቹን የጡረታ መዋጮ ከደመወዛቸው ቀንሶ እና የራሱን መዋጮ ጨምሮ ለጡረታ ፈንዱ በየወሩ የመክፈል ግዴታ አለበት።
የጊዜ ገደብ፦ የጡረታ መዋጮው ለሠራተኞች የወር ደመወዝ ከተከፈለበት ወር መጨረሻ ቀን አንስቶ በ30 ቀናት ውስጥ ለፈንዱ ገቢ መደረግ አለበት።
አስተዳደርና ቁጥጥር፦ ፈንዶቹን የማስተዳደር ኃላፊነት የ"መንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር" ሲሆን፣ ክፍያዎችን በወቅቱ ገቢ ባላደረጉ ተቋማት ላይ ኦዲት የማድረግ፣ ንብረት በጨረታ የመሸጥ፣ እንዲሁም ከባንክ ሂሳባቸው ላይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የመቀነስ ሰፊ የሕግ ሥልጣን ተሰጥቶታል።
 
🔹 6. የአክቹዋሪ ግምገማ (Actuarial Analysis and Evaluation)
የአክቹዋሪ ግምገማ ማለት የጡረታ ዐቅድ ስታቲስቲካዊ መረጃዎችን፣ የኢንቨስትመንት አፈጻጸምን፣ የኢኮኖሚ እና ሥነ-ሕዝብ ግምታዊ መረጃዎችን በመተንተን የፈንዱን የወደፊት የመክፈል አቅምና ስጋቶች አስቀድሞ የሚያሰላ ሳይንሳዊ ዘዴ ነው። በአዋጁ አንቀጽ 15 መሠረት፣ የመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ ዐቅድ የረጅም ጊዜ አስተማማኝነቱን ለማረጋገጥ በየአምስት (5) ዓመቱ በሂሳብ ስሌት ባለሙያዎች (Actuaries) እንዲገመገም ይደረጋል።
 
📢 መልእክታችን፦
"በሕግ የተደገፈ የጡረታ መዋጮ፤ የዛሬ ተዓማኒነት፣ የነገ አስተማማኝ ሕይወት!"
ስለ መብትና ግዴታዎ ይረዱ፤ ተቋማትም መዋጮዎችን በወቅቱ ገቢ በማድረግ የሠራተኛውን የነገ ተስፋ ያለምልሙ።
 
#የጡረታአዋጅ #አዋጅ1267 #ማኅበራዊዋስትና #የመንግሥትሠራተኞች #የጡረታፈንድ #የአክቹዋሪግምገማ #ኢትዮጵያ

Share this Post