አስተዳደሩ የ2019 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙን ገመገመ

የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር የ2019 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ አካሄደ። በመድረኩ ላይ የአስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሸጉ ኬሎ ተገኝተው፣ የተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎችን አፈጻጸም የገመገሙ ሲሆን በቀጣይ ትኩረት የሚሹ አቅጣጫዎች ላይም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በግምገማ መድረኩ ላይ እንደተገለጸው፣ የሰዓት አጠቃቀምን እና ዕቅድን በየጊዜው ከመገምገም አንጻር አበክሮ መሠራት አለበት። ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሸጉ ኬሎ “ጊዜ የለም” የሚለው አመለካከት ከራሳችን አእምሮ የሚመነጭ እንጂ፣ በቁም ነገር ተሠርቶ ሰዓትን በአግባቡ ከተጠቀሙ ሰፊ ጊዜ እንዳለ ገልጸዋል። እንዲሁም ሥራዎች በውዝፍ እንዳይያዙ በዕቅድ መመራትና በምክንያት ላይ ብቻ ከመመካት ይልቅ በውጤት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማረጋገጥ የመረጃ ማጥራቱ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያሻው ተጠቁሟል። አቶ ሸጉ ኬሎ እንዳሉት፣ የጠራ መረጃ እጃችን ላይ መያዝ ወሳኝ መሆኑን አንስተው፤ ሠራተኞች ከባንኮችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መረጃዎችን በአግባቡ ማደራጀት፣ የባለ መብቶችን ጥያቄዎች በብቃት መመለስ እና ተገልጋዮች እንዳይጉላሉ በቅርርብ መከታተል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በአገልግሎት አሰጣጡ ሂደት ውስጥ ቴክኖሎጂንና ሪፎርምን ማቀናጀት እንደሚያስፈልግ የተገለጸ ሲሆን፣ ሠራተኞችን ለዘመናዊ አሠራር የማብቃትና የዲጂታል ሲስተሞችን የመጠቀም አቅም ማሳደግ ላይ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ተቋሙ ያስቀመጣቸውን ግቦች ለማሳካትም ሁሉም ሠራተኛና የሥራ ኃላፊ በባለቤትነት ስሜት፣ በቁርጠኝነት እና በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባ አቶ ሸጉ ኬሎ አሳስበው፤ በቀጣይ በሂደት ላይ ያሉ ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የተሻለ ተቋማዊ ውጤት ለማምጣት ጥረት ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ በቀረበው ሪፖርት እንደተገለጸው አስተዳደሩ ለመንግስት ሠራተኞች የጡረታ መለያ ቁጥር የመስጠት፣ ለአዳዲስ ባለመብቶች የጡረታ አበል የመወሰን፣ በተቋሙ አሠራሮች ላይ ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ የመስጠት፣ በአሠሪ መ/ቤቶች ላይ የመዋጮ ምርመራ የማካሄድ፣ በተለያዩ የመረጃ መስጫ መንገዶች ለተገልጋዮች መረጃ የመስጠት እና ሌሎችም ተከናውነዋል የተባለ ሲሆን፣ በሩብ ዓመቱም አስተዳደሩ የዕቅዱን 94 በመቶ አከናውኗል ተብሏል።

ለሦስት ቀናት በተካሄደው የዕቅድ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ ላይ የአስተዳደሩ አመራሮች፣ የስራ ኃላፊዎችና የሪጅን ጽ/ቤቶች ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

Share this Post