የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር 21ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በፓናል ውይይት አከበረ
አዲስ አበባ፣ ኅዳር 18/2019 ዓ.ም (የመ.ሠ.ማ.ዋ.አ)
የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር 21ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን «በብዝኃነት የደመቀች፤ በምክክር የጸናች ሥልጡን ኢትዮጵያ» በሚል መሪ ሃሳብ በዛሬው ዕለት በደማቅ ሁኔታ አክብሯል።
በዓሉን በንግግር የከፈቱት የአስተዳደሩ የኮርፖሬት ሪሶርስ ማኔጅመንት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን በቀለ፤ አገራዊ አንድነት ማለት ልዩነቶችን በማጥፋት የሚመጣ ወጥነት ሳይሆን ልዩ ማንነቶች ተከብረውና ተሰናስለው የሚኖሩበት ብዝኃነትን ያቀፈ አንድነት መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም አስተዳደሩ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ቢሠራና ቢዘዋወር የጡረታ መብቱ ተጠብቆለት በእኩልነት የሚስተናገድበት የአንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ሕያው ተምሳሌትና ተቋማዊ ድልድይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመቀጠልም «የብዝኃነት አስተዳደር እና የመንግሥታት ግንኙነት ለጠንካራ የፌዴራል ሥርዓት ግንባታ» በሚል ርዕስ ለተሳታፊዎች የቀረበውን መነሻ ሰነድ መሠረት በማድረግ፣ በአስተዳደሩ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሸዋንግዛው ታየወርቅ አወያይነት ሰፊ ውይይት ተካሂዷል። የዋናው መሥሪያ ቤት እና የአሥሩም ሪጅኖች የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በተሳተፉበት በዚህ መድረክ፤ የፌዴራል ሥርዓቱ ዋና ግብ ብዝኃነትን ያቀፈ አንድነትን መገንባት መሆኑ ተነስቷል። ለዚህም ሥርዓቱን ይበልጥ ለማጠናከር በየደረጃው ያለውን ተቋማዊ ቅንጅት ማጎልበትና ፌዴራላዊ አስተሳሰብን ማዳበር ወሳኝ ሚና እንዳለው ተመላክቷል።
በመጨረሻም አቶ ሸዋንግዛው ታየወርቅ በሰጡት የማጠቃለያ ንግግር፤ በአስተዳደሩ ውስጥ የብዝኃነት መስተንግዶን በማጠናከር ለሁሉም ተገልጋዮችና ባለመብቶች ከቋንቋ፣ ከባህልና ከአካባቢ ልዩነት ባሻገር ቀልጣፋና ፍትሐዊ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል። እንዲሁም አመራሩና ሠራተኛው በሥራ አካባቢ የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን በምክክርና በመግባባት በመፍታት «ሥልጡን ኢትዮጵያን» እውን ለማድረግ የበኩላቸውን ታሪካዊ አሻራ እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።