አስተዳደሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የዕቅዱን 95 በመቶ ማከናወኑ ተገለፀ

አስተዳደሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የዕቅዱን 95 በመቶ ማከናወኑ ተገለፀ
============//============
የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም የግምገማ መድረኩን ከሐምሌ 21 - 25/2017 ድረስ በጅማ ከተማ አከሂደዋል። በዚህ የዕቅድ አፈጻጸም መድረክ ላይ እንደተገለጸው በስራ ላይ ያሉ የመንግስት ሠራተኞች በመመዝገብ በ2017 ዓ/ም 178,108  ሠራተኞች የማህበራዊ ዋስትና መለያ ቁጥር መሰጠቱ ተገልጸዋል። 

በሌላ በኩል ለጡረታ አበል ውሳኔ የሚያስፈልጉ ማስረጃዎች የተሟሉ መሆናቸውን በማረጋገጥ ለ 74,182 ባለመብቶች የአበል ውሳኔ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን አፈፃፀሙ ከ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር 13.3% ዕድገት ማሳየቱ ተነግሯል። 

አስተዳደሩ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች መረጃ ከመስጠት አኳያ በአዋጅና መመሪያዎች ላይ ከ3,737 የመንግስት መ/ቤቶች ለተወከሉ 12,107 የሰው ሀብት እና የፋይናንስ ኃላፊዎች እንዲሁም ባለሙያዎች ግንዛቤ ተሰጥቷል። 

በተጨማሪም ለተገልጋዮች መረጃ ተደራሽ ለማድረግ በመረጃ ዴስክ፣ በመገናኛ ብዙሃን፣ በመደበኛ ስልክና በመረጃ ማዕከል (ነጻ መስመር 8926) ፣ በህትመት እና በማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ለ3.2 ሚሊየን ተገልጋዮች መረጃ መሰጠቱ ተነግሯል፡፡

በመድረኩ ላይ እንደተገለጸው የጡረታ መዋጮ በአግባቡ መሰብሰቡን ለማረጋገጥ በ5,118 የመንግስት መ/ቤቶች ላይ የገቢ ምርመራ መከናወኑን እና በወቅቱ ያልገባ የጡረታ መዋጮ ምርመራ በማድረግ ከተገኘው ገንዘብ 99% ገቢ መደረጉ የተነገረ ሲሆን በአጠቃላ አስተዳደሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የዕቅዱን 95 በመቶ ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ገቢን ለማሳደግ ከመንግስት ዋስትና ሰነዶች፣ ከጊዜ ገደብ ተቀማጭ፣ ከሪልስቴት፣ ለባንኮች ከተላለፈው የጡረታ አበል ቅድመ ክፍያ እና ከአክሲዮኖች ላይ ገቢ መገኘቱ የተገለፀ ሲሆን በተያዘው በጀት ዓመት የሪፎርም ስራዎችን ለማጠናከር የውጤት ተኮር አፈፃፀም ምዘና መመሪያ፣ የመልካም አስተዳደር ትግበራ ዕቅድ እና የኢንቨስትመንት ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ተገልፀዋል። በተለይም የሶፍትዌር ልማትና መረጃ ቋት ግንባታ፣ የንብረት አስተዳደር እና የትምህርትና ስልጠና መመሪያ በማዘጋጀት ስራ ላይ በማዋል አፈጻጸም እንዲያድግ የሚደረግ መሆኑን ተነግሯል። 

ከጡረታ ባለመብትነት ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ቅሬታዎች በሚመለከት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለተጨማሪ ወጪ እና ለእንግልት እንዳይዳረጉ በአካል መቅረብ ሳይጠበቅባቸው በቨርቿል በአካባቢያቸው ሆነው ጉዳያቸውን በማስረዳት ምላሽ መሰጠቱንም ተነግሯል። 

በዚህ የዕቅድ ግምገማ ለቀጣይ በጀት ዓመት ክፍተት ሊሞሉ የሚችሉ የተለያዩ ስልጠናዎች የተሰጡ ሲሆን በተለይ የሥነ-ምግባራዊ አመራርነት ለተቋማዊ ተልዕኮ ስኬት ሥልጠና፣ በንብረት አስተዳደርና ዋጋ ትመና ስልጠና እንዲሁም በውጤት ተኮር ትግበራ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል፡፡  

ለአምስት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው የዕቅድ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ ላይ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዋናው መስሪያ ቤትና የሪጅን ጽ/ቤቶች ኃላፊዎች እንዲሁም የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

Share this Post