የመንግስት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ወደ ዲጂታላይዜሽን ለመሸጋገር የሚያስችለውን የTier-III ሞዱላር ዳታ ሴንተር ፕሮጀክት በይፋ ተረከበ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም — የመንግስት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር (PSSSA) የአገልግሎት አሰጣጡን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ እንዲሁም ተቋማዊ ሪፎርሙን በቴክኖሎጂ ለማገዝ ያስገነባውን ባለከፍተኛ ጥራት የTier-III ሞዱላር ዳታ ሴንተር (Modular Data Center) ፕሮጀክት ርክክብ ዛሬ በይፋ ፈጽሟል።ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት (EAII) በዋና ተቋራጭነት ሲያጠናቅቀው፣ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (ASTU) ደግሞ በቁጥጥርና አማካሪነት በጋራ ሰርተውታል።
 
በምረቃና ርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሸጉ ኬሎ እንደገለጹት፣ ይህ የዳታ ሴንተር ግንባታ መጠናቀቅ አስተዳደሩ ወደ ዲጂታላይዜሽን ለመግባት ለጀመረው ጉዞ ትልቅ ማሳያና አንድ እርምጃ ወደፊት የተራመደበት ታሪካዊ ክስተት ነው። ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለውም፦ "ይህ በቴክኖሎጂ የታገዘ የዳታ ሴንተር መገንባት ተቋማችን ለዓመታት ሲያከናውን የቆየውን ሰፊ የሪፎርም (የለውጥ) ስራ ይበልጥ ወደላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው። የአገልግሎት አሰጣጣችንን ግልጽ፣ ፈጣን እና ተደራሽ በማድረግ የተገልጋይ ማህበረሰባችንን እርካታ በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል" ብለዋል።
 
ይህ ዘመናዊ የTier-III ደረጃውን የጠበቀ የዳታ ሴንተር ለአስተዳደሩና ለተገልጋዮች በርካታ ዘላቂ ጥቅሞችንና የአገልግሎት ፋይዳዎችን ያስገኛል። የጡረታ ባለመብቶችና የመንግስት ሰራተኞች መረጃዎችን በአንድ ማዕከል በማደራጀት ቀደም ሲል የነበሩ መረጃዎችን በአስተማማኝ ሁኔታ ወደ አዲሱ ሲስተም (Migration) ለማዘዋወር የሚያስችል ሲሆን፣ ይህም የጉዳይ ማስተናገጃ ጊዜን እጅግ በማሳጠር ቀልጣፋና ፈጣን የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሰፍን ያደርጋል። ከዚህም በላይ የዜጎችን ሚስጥራዊ የጡረታና የማህበራዊ ዋስትና መረጃዎች ከተለያዩ የሳይበር ጥቃቶችና አደጋዎች በአስተማማኝ ሁኔታ የሚጠብቅ ባለከፍተኛ ጥራት ቴክኖሎጂ የተገጠመለት በመሆኑ፣ ተቋሙ ወደ ወረቀት አልባ (Paperless) አሰራር ለሚያደርገው ሽግግርና ለውስጥ የአሰራር ሪፎርም እንደ ዋና የጀርባ አጥንት ሆኖ ያገለግላል።
 
አቶ ሸጉ ኬሎ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ላይ ይህንን ግዙፍና ውስብስብ የቴክኖሎጂ ፕሮጀክት በተቀመጠለት ጊዜና ጥራት አጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ላደረገው ለዋና ተቋራጩ ለኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት (EAII) እንዲሁም የቁጥጥርና የሙያ እገዛ ላደረገው ለአማካሪው ለአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (ASTU) የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
 
የሀገር በቀል ተቋማትን እምቅ የቴክኖሎጂ አቅም ያሳየ ፕሮጀክት መሆኑን የጠቀሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ አስተዳደሩ በቀጣይም በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የታገዙ አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት የዜጎችን ማህበራዊ ዋስትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

Share this Post