20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በድምቀት ተከበረ
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በድምቀት ተከበረ
የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር አመራሮችና ሠራተኞች 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ ሕዳር 30 ቀን 2018 በድምቀት አከበሩ።
በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ የኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን በቀለ እንዳሉት በየዓመቱ ህዳር 29 የሚከበረው ይህ በዓል ዓላማው በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል በዴሞክራሲያዊ መግባባት ላይ የተመሰረተ አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር በማድረግ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ማጎልበት ነው።
ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባለቤት ነች፡፡ ከዚህ የተነሳ ለዘመናት የቆዩ ከብዝሃነት ጋር ተያይዞ የሚመነጩ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች አሉ። ለነዚህ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችል ብዝሃነትን ከአንድነት ያስተሳሰረ ህብረ ብሔራዊ ፌደራላዊ ስርዓት ተመስርቷል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብትን መከበር ያረጋገጠው የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት ህዳር 29 ቀን 1987 መፅደቁን ያስታወሱት ም/ዋና ስራ አስፈጻሚው ይህ ቀን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መብት መከበር ሕገ መንግስታዊ ዋስትና የተረጋገጠበት መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም በሕገ መንግስቱ የሀገሪቱ የስልጣን ባለቤት ሕዝብ መሆኑን በግልጽ መስፈሩንና ስልጣን የሚያዘውም በምርጫ ብቻ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎም በአጀንዳነት የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችን ወደ ውይይት ጠረጴዛ በማምጣት ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በርካታ ጥረቶች መደረጋቸውንና በዚህም አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸው የሚታይ ሐቅ ነው ብለዋል።
በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 90 ንኡስ አንቀጽ 1 መሠረት ዜጎች የማህበራዊ ዋስትናቸው እንዲረጋገጥና ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት ለአስተዳደራችን የተሰጠ ተግባር መሆኑን የጠቀሱት ም/ዋና ስራ አስፈጻሚው በህገ-መንግስቱ የተሰጠንን ተልዕኮ በማሳካት እና ለሀገር ዕድገት የራሳችን ድርሻ ለማበርከት የበኩላችን መወጣት ይገባል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዕለቱም ዴሞክራሲ እና የፌዴራል ሥርዐት በኢትዮጵያ፣ ተስፋዎቹ እና ተግዳሮቶቹ በሚል ርዕስ በቀረበው ሠነድ ላይ ውይይት አካሂደዋል።
በዋናው መ/ቤት በተከበረው በዚህ በዓል ላይ የአስተዳደሩ አመራሮች፣ የዋናው መ/ቤትና የመሀል ሪጅን ጽ/ቤት የስራ ኃላፊዎችና ሠረተኞች ተገኝተዋል።
://**
ህዳር 30 /2018 ዓ.ም